ቀጥታ፡

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ለበሽታ ቅድመ መከላከል ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2017(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን መከላከል እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በምርመራ በመለየት ለቅድመ መከላከል ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመሆን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የጤና ምርመራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

አገልግሎቱ "በጎ ፈቃደኝነት ለጤናማ ማህበረሰብ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጤና ምክር፣ ምርመራና ህክምና የሚሰጥበት ነው።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጤናው ዘርፍ በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።


 

እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ ምርመራ በማድረግ የመለየትና የቅድመ መከላከል ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ መገናኛ ብዙኃን እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ በየዓመቱ እያደገ የመጣውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

የአዲስ አበባ የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ለሚሰጠው የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ብለዋል።

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ፥ አገልግሎቱ የጤና ባለሙያዎች በጎነትን በተግባር የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።


 

ሆስፒታሉ ላለፉት ሶስት ዓመታት ከፍለው መታከም ለማይችሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የክረምት በጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፥ ዘንድሮም ይህንኑ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል  ነው ያሉት።

በበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ተሳታፊ የሆኑት ዶክተር የትናየት በቀለ እና ዶክተር ነብዩ ዛራ፥ ከፍለው መታከም ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎት በመሳተፋቸው የህሊና እርካታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።


 

ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ሊቀ ትጉሃን ያሬድ አበበ የአይን ምርመራ ለማድረግ መምጣታቸውንና በሀኪሞቹ ምክር ሙሉ የጤና ምርመራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉ የሚበረታታና ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው ብለዋል።  


 

ወይዘሮ እታገኝ ትርፌ በበኩላቸው በጤና ባለሙያዎቹ ልጃቸው ነጻ የተለያዩ የጤና ምርመራዎች እንደተደረገለት ገልፀዋል።

የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎቱ በህክምና ወጪ ምክንያት ሳይታከሙ በየቤቱ ላሉ ሰዎች ትልቅ እፎይታ የፈጠረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ግርማ አለማየሁ ናቸው።

 

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም