በመዲናዋ 44ሺህ 45 ሜትር ኪዩብ የኮንሶ እርከን ተሰርቷል - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት አመት 44ሺህ 45 ሜትር ኪዩብ የኮንሶ እርከን መሰራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በ2017 በጀት አመት የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ እንደገለጹት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችልና ስነምህዳሯ የተጠበቀ ከተማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።


 

የኮንሶ ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም የአፈርና የውሃ እቀባዎች መሰራቱን አንስተው ለቱሪስት መስህብነትም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በባህላዊው የእርከን ስራው ከ600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በዚህም 44ሺህ 45 ሜትር ኪዩብ የኮንሶ እርከን ተሰርቷል ብለዋል።

ከእንጦጦ ወንዝ እስከ ራስ መኮንን ድልድይ በወንዙ ግራና ቀኝ አካባቢዎች፣ የቀበና ወንዝ፣ በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ በጎሮና ሌሎች አካባቢዎች የእርከን ስራዎቹ መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በወንዞች ዳርቻ የአፈር መከላትን ለመከላከልና ጎርፍን መቀነስ የሚያስችል በኮንሶ ባህላዊ አሰራር የጋብዮን ግንብ 7ሺህ 786 ሜትር ኪዩብ መገንባቱንም አክለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ በተፋሰስ ልማትና የወንዞች ዳርቻም ከቀበና እና እንጦጦ ወንዞች እስከ ፒኮክ አካባቢ ድረስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ተከናውኗል።

438 ሄክታር የተጎዱ ቦታዎች ተለይተው የዝናብ ማቆሪያ፣ የድንጋይና የአፈር ክትር ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉም ገልጸዋል።


 

በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞችን በማጽዳት ብክለትን የመከላካል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የወንዞች ልማትና ብክለትን ለመከላከል የወጣው ደንብ ላይ ለተለያዩ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መሰራታቸውንም ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ወንዞችን በበከሉ አካላት ላይ ከ2ሸህ እስከ 1 ሚሊየን ብር የሚደርስ የቅጣት እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም