የደንብ ጥሰት የፈጸሙ ከ3 ሺህ 200 በላይ ተቋማት እርምጃ ተወስዶባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የደንብ ጥሰት የፈጸሙ ከ3 ሺህ 200 በላይ ተቋማት እርምጃ ተወስዶባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2017(ኢዜአ)፦ የአየር እና የድምጽ ብክለት ህግን የተላለፉ ከ3 ሺህ 200 በላይ ተቋማት እርምጃ እንደተወሰደባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በ2017 በጀት አመት የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት አመት በከተማው የአካባቢ ፣ የድምፅና ፍሳሽ ብክለት እንዲሁም የአማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነሰ የሚያስችሉ የቁጥጥር ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ14 ሺህ 800 ተቋማት በላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች መከናወኑን አንስተዋል፡፡
ተቋማቱ በአካባቢ ላይ የድምጽና የአየር ንብረት ብክለት እንዳያስከትሉ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል መደረጉን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው ያላስተካከሉት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ነው የተናገሩት።
የደንብ ጥሰት በፈጸሙ 3 ሺህ 249 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በዚህም የተለያዩ ፋብሪካዎች፣ የምሸት ጭፈራ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
በተወሰደው ህጋዊ እርምጃም ለ3 ሺህ 66 ተቋማቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን 183 ተቋማት ደግሞ እንዲታሸጉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በወንዝና ወንዝ ዳርቻ ላይ ብክለት ባደረሱ ተቋማት ላይ ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ቅጣት መጣሉንም አክለዋል።