ለህዝብ ተጠቃሚነት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል የድጋፍና ቁጥጥር ሥራችንን እናጠናክራለን-የክልሉ ምክር ቤት አባላት

ወልቂጤ፤ሐምሌ 30/2017( (ኢዜአ) )፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለህዝብ ተጠቃሚነት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል የድጋፍና ቁጥጥር ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከተገኘው ልምድ በመነሳት በበጀት ዓመቱ የተሻሉ የልማት ተግባራት እንዲከናወኑ ከምክር ቤት ጉባኤ ባለፈ በመስክ ምልከታ ድጋፍና ቁጥጥር በማድረግ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ በመስክ ምልከታ ጭምር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ጌታሁን ነጋሽ፣ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በከተማና በገጠር መከናወናቸውን ተናግረዋል።


 

ህብረተሰቡ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተሞች እና በገጠር የተጀመሩ የኮሪደር ልማት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች፣ ተዘዋዋሪ ችሎት እንዲሁም ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የበለጠ እንዲጠናከሩ የድጋፍ፣ ክትትል እና ቁጥጥር ስራቸውን እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል።

አቶ ግዛቸው ዋሌሬ የተባሉ ሌላው የምክር ቤት አባል እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደምክር ቤት አባል የበኩላቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።


 

ክልሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰው፣ ቀሪ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተለይ አስፈጻሚ ተቋማት የህዝብ ጥያቄን ለመመለስ የሚያናውኗቸውን ተግባራትን አፈጻጸም የመከታተልና የመደገፍ ሚናቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ነው ያረጋገጡት።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመስኖ ልማት፣በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች ዘርፎች በተከናወኑ ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

በአስፈጻሚ አካላት የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ድጋፍና ክትትላቸውን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አሌይካ ሽኩር ናቸው።


 

በተለይ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደምክር ቤት አባል በመስክ ጭምር በማረጋገጥ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

ግብርናን ለማሳደግ በመስኖ ልማት የተመዘገበው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረውና በትምህርት ለትውልድ ኢኒሼቲቭ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ሌላኛው ምክር ቤት አባል ሀጂ ገራድ ድልታታ በበኩላቸው፥ በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች አርሶ አደሩ የልፋቱን ውጤት እንዲያስገኙ በገበያ ትስስር የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።


 

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደተከናወኑ በተጨባጭ ማየታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም