ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጡ ነው

ጊምቢ፤ሀምሌ፤30/2017 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጡ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ የማልበስና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመከላከል አላማ ሰንቆ ባለፉት ሰባት ዓመታት እየተከናወነ ነው።

በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ የማምጣትና ከችግር የመውጫ አንዱ መንገድ ተደርጎ የተወሰደው ይኸው መርሃ ግብር በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።

በዚህም መሰረት ዘንድሮ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዞ  714 ነጥብ 7 ሚሊዮን በማሳካት አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል።  

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ ሀገር ስኬት እየተመዘገበበት ጥቅሙም እየተገለጠ መምጣቱን በርካቶች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

በምዕራብ ወለጋ ዞንም የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኤሊያስ ለሚ፣ አቶ ባልይና ተርፋ እና አቶ ጸጋዬ ተሰማ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐግብር በጋራ ሰርተን በጋራ የምንጠቀምበት ሃብት መሆኑን በተግባር እያረጋገጥን ነው ብለዋል። 


 

በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የቡና ልማት ተጨባጭ ውጤት የታየበት መሆኑን አንስተዋል።


 

ለአካባቢ ጥበቃና እንስሳት የመኖ አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አሻራው በጉልህ መታየቱን ገልጸው ልማቱን አጠናክረን እንቀጥላልን ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ  ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ጥቅም በተግባር እየታየና ተጠቃሚዎችም ምስክርነታቸውን እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

በለውጡ ዓመታት በብዙ መልኩ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች ተተክለው ለውጤትም መብቃታቸውን ገልጸው በዞኑ ዘንድሮ ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች መሸፈኑን አረጋግጠዋል።


 

የልማት ስራው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው ችግኞችን በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም