የአፍሪካ ከተሞች ለአደጋ አቅም እንዲገነቡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው- የአፍሪካ ህብረት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ከተሞች ለአደጋ አቅም እንዲገነቡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው- የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት አደጋን የሚቋቋሙ ጠንካራ የአፍሪካ ከተሞች እንዲገነቡ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የአፍሪካ የማይበገር ከተማ ፕሮግራም (AURP) በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።
የከተማ ፕሮግራሙ የመጀመሪያ የስትሪንግ ኮሚቴ እና የቴክኒካል ቡድኖች ስብስባ ከነሐሴ 8 እስከ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ይካሄዳል።
ስብስባው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከደቡብ አፍሪካ መንግስት፣ ከደቡባዊ አፍሪካ ልማት ትብብር ኮንፈረንስ (ሳዴክ) እና ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመሆን በጋራ ያዘጋጀው ነው።
የአፍሪካ ህብረት ተቋማት እና አደረጃቶች አመራሮች፣ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኃላፊዎች፣ የህብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የከተማ ልማት ባለሙያዎች በስብስባው ላይ ይሳተፋሉ።
የአፍሪካ ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ፣ አደጋ ፣ የመሰረተ ልማት አደጋዎች እና ፈጣን እድገትን መቋቋም የሚችል የማይበገር አቅም መገንባት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው ስብስባ በአፍሪካ የከተማ አይበገሬነትን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የሚያግዝ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም "ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በዚሁ ፎረም ላይ የአፍሪካ የማይበገር ከተማ ፕሮግራም (AURP) ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።
በኬፕ ታውን የሚደረገው ስብስባ ፕሮግራሙ ይፋ ከተደረገ ጊዜ አንስቶ ያለውን አፈጻጸም ይገመግማል።
አይበገሬ ከተሞችን ለመገንባት ከተለመደው የፋይናንስ አሰባሰብ ውጪ አዳዲስ አማራጮችን መጠቀም ላይ ምክር ሀሳቦች ይቀርባሉ።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች እና የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባት ሁኔታ ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የአፍሪካ ህብረት ከተሞች የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመቋቋም አቅማቸው እንዲጠናከር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ የማይበገር ከተማ ፕሮግራም የዚህ ስራ አካል እንደሆነ አመልክቷል።
ፕሮግራሙን አስመልክቶ የሚደረገው ስብሰባም በአፍሪካ ዘላቂ እና አደጋን የሚቋቋሙ ከተሞችን ለመገንባት ለተያዘው ውጥን የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት በመረጃው አስፍሯል።