የወቅቱ የቻን አሸናፊ ሴኔጋል ክብሯን የማስጠበቅ ጉዞዋን በድል ጀምራለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) በምድብ አራት በተደረገ ጨዋታ ሴኔጋል ናይጄሪያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።


ማምሻውን በዛንዚባር አማኒ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ክርስቲያን ጎሚስ በ75ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።


ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ሴኔጋል ምድቡን በሶስት ነጥብ መምራት ጀምራለች። ናይጄሪያ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች።


በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ኮንጎ ብራዛቪል እና ሱዳን አንድ አቻ ተለያይተዋል።


ታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ በጣምራ ያዘጋጁት ውድድር ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።


በሻምፒዮናው ላይ 19 ሀገራት በአራት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል። ውድድሩ እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።


በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን የሚያነሳ ሀገር የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚያገኝ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

አጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን ይህም አልጄሪያ ላይ ከተካሄደው ሰባተኛው የቻን ውድድር የ32 በመቶ ብልጫ አለው።


ታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደው 36ኛውን የአፍሪካ ዋንጫም በጋራ ያዘጋጀሉ። የቻን ውድድር ለሀገራቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት የሚያገለግል ነው ተብሏል።


እ.አ.አ በ2009 የተጀመረው ቻን በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ነው። ይህም ሀገር በቀል ተጫዋቾች የሚያገኙትን የጨዋታ እድል መጨመር ያለመ ነው።


ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሞሮኮ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሱ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ እና ሴኔጋል ቀሪ አሸናፊ ሀገራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም