የቀጣዩ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ጥቅል ክፍያ ጣሪያ 70 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ተወሰነ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦  በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለብ የጥቅል ክፍያ ጣሪያ 70 ሚሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሰባተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ አድርጓል።

በጉባኤው ላይ ሁለት አጀንዳዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል። 

የመጀመሪያው አጀንዳ የክለቦች ክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ  ማሻሻያ እንዲደረግበት የቀረበ ሀሳብ ሲሆን መመሪያው የተለያዩ ግብዓቶች  ታክለውበት እንዲሻሻል ተወስኗል። 

ሌላኛው የጉባኤው ተሳታፊዎች ትኩረት የሳበው አጀንዳ የክለቦች ጥቅል ክፍያ ጣሪያ ነው።
አክሲዮን ማህበሩ ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም የክፍያ ጣሪያ አማራጮችን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጥቅል ክፍያ ጣሪያ ላይ ጉባኤው ከተወያየ በኋላ የ2018 ዓ.ም የክፍያ ጣሪያ በክለብ ደረጃ 70 ሚሊዮን እንዲሆን በአብላጫ ድምፅ መፅደቁን የአክሲዮን ማህበሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም