በህገ መንግስት አጣሪ ጉዳዮች ባሉ ክርክሮች የሚነሱ ነጥቦችን መሰረት አድርጎ ምርምሮችን ማካሄድ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦በህገ መንግስት አጣሪ ጉዳዮች ባሉ ክርክሮች የሚነሱ ነጥቦችን መሰረት አድርጎ የሚካሄዱ ምርምሮች የህብረተሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።

የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት በተስማሙበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ምርምሮች ለህገ መንግስታዊነትና ለህግ አስተምህሮ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት፤ በህገ መንግስት አጣሪ ጉዳዮች ባሉ ክርክሮች የሚነሱ ነጥቦችን መሰረት አድርጎ የሚካሄዱ ምርምሮች ተጽዕኖ ከመፍጠራቸውም በላይ የህብረተሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ይሆናሉ።

የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት በህገ-መንግስት ጉዳዮች ላይ በሚሰጥ ውሳኔ ላይ ምክረ ሃሳብ እና ውሳኔ የሚሰጥ ትልቅ ሃላፊነት ያለበት አካል መሆኑን የገለጹት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ፤ በተቋሙ የሚሰጡ ውሳኔዎች የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።  

እነዚህን ለመወሰን የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ ይህም ለህገ መንግስት እና ለህግ አስተምህሮ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ባለፉት ዓመታት በፍትህ ስርዓቱ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን እያፈራ ይገኛል።


 

ትምህርት ቤቱ የፍትህ ስርዓቱና የህግ ማዕቀፉ እንዲዘምን በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል። 

የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወይሳ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ጥራት ተደራሽ እና ቀልጣፋ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል የጥናትና ምርምር ስራዎች ያከናውናል፡፡


 

በተቋሙ ጥናትና ምርምር የሚፈልጉ ፈርጀ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመው፤  እነዚህ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከዩንቨርሲቲው ጋር የተደረገው ስምምነቱ ትልቅ ሚና አለው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ክፍል ተጠባባቂ ዲን ፕሮፌሰር ሙራዱ አብዶ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ወደ ተቋሙ መምህራንን የማሰማራት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራ የመሳተፍ ተግባር ያከናውናል።


 

ተቋሙ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያገኙ እገዛ እንደሚያደርግም ፕሮፌሰር ሙራድ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም