በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስታትስቲክስ መረጃና የሲቪል ምዝገባ ሥርዓት እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስታትስቲክስ መረጃና የሲቪል ምዝገባ ሥርዓት እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ከተባበሩት የስነህዝብ ፈንድ ጋር በመተባበር የስታትስቲክስ መረጃ እና የሲቪል ምዝገባ ሥርዓትን የማዘመን ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክ አገልግሎት ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ(UNFPA) የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ መረጃና የሲቪል ምዝገባ ስርዓትን ለማዘመን የሚያግዝ ድጋፍ አግኝቷል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የተመድ የስነ ህዝብ ፈንድ ለረጅም ጊዜ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አገልግሎቱ የኢትዮጵያን ስታቲስቲክስ መረጃና የሲቪል ምዝገባ ሥርዓትን ለማዘመን ለሚሰራቸው ስራዎች የሚያግዙ የዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።
በድጋፍ የተሰጡ ኮምፒውተሮች ለክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች እንደሚሰራጩ ጠቅሰው ለረጅም ጊዜ የቆየው የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሥነ-ህዝብ ፈንድ (UNFPA) ተወካይ ታይዎ ኦልሚዮ በበኩላቸው ተቋማቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት እንዳለው ገልፀዋል።
ተቋማቸው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ መረጃና የሲቪል ምዝገባ ሥርዓትን ለማዘመን እየተከናወኑ ለሚገኙ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዛሬ የተደረገው የኮምፒውተር ድጋፍ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ለጀመራቸው ስራዎች አጋዥ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።