የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም መሰረተ ልማትን በማሟላት ለዘርፉ እድገት ገንቢ ሚናውን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም መሰረተ ልማትን በማሟላት ለዘርፉ እድገት ገንቢ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱን በ2024/25 ወይም በ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። 


 

የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍና አገር ውሰጥ በረራ አድማሱን በማስፋት በበጀት ዓመቱ ከ19 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን አጓጉዟል፡፡

አየር መንገዱ 21 የአገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች እንዳለው ገልጸው፤ ሌሎች አምስት አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህም ደብረ ማርቆስ፣ ያቤሎ፣ ሚዛን አማን፣ ነገሌ ቦረና እና ጎሬ መቱ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሁሉም ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ አየር መንገዱን ማዘመን የሚያስችሉ አዳዲስ ተርሚናሎች በባህር ዳር፣ ሽሬ፣ ደንቢዶሎ እና ነቀምት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገራዊ የቱሪዝም ዘርፉን ሽፋን ማሳደግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አራት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጂዎችን እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጸው፤ ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶችን የኢትዮጵያ ቆይታ ለማራዘም ያግዛሉ ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ በ"ኢቲ ሆሊዴይስ" አማካኝነት መንገደኞች በአዲስ አበባ ሲያልፉ ጎብኝተው የሚሄዱበት አሰራር ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዘመናዊ ሎጂዎችና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ለሚሄዱ ጎብኝዎች የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች ግዥ መከናወኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ ምቹና ቀለል ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች በሐይቅና በየብስ ላይ ማረፍ የሚችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በሚቀጥለው ጥቅምትና ጥር  2018 ዓ.ም እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም