በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ነው

ዲላ ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአፈር ለምነት በመጨመር የግብርና ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ የግብርና ቢሮ አመራር እና ሠራተኞች በዲላ ከተማ አስተዳደር ጎላ ቀበሌ በሚገኘው ቱሉ ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ የልማት ሥራዎች ለትውልድ የሚተርፉ ናቸው።
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የአፈር ለምነት በመጨመር የግብርና ምርታማነትን እያሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በጌዴኦ ዞን የቡና ምርታማነት ላይ የታየው ለውጥ ለእዚህ አንድ ማሳያ መሆኑንም መሪሁን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን አጠናክሮ በማስቀጠል ለቀጣይ ትውልድ የለመለመ አካባቢን ለማውረስና የግብርና ምርታማነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንሰራለን ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የከተማቸውን ገጽታ እየቀየረ መምጣቱን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ናቸው።
የአረንጓዴ ልማቱ በተለይ በከተማዋ በተካለሉ አካባቢዎች የሚገኙ ተራራማና ተዳፋታማ ቦታዎችን ለማልማት ከማስቻሉ በተጨማሪ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እያስቻሉ ነው ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሪት አዲስ አብርሃም በበኩሏ ችግኝ ተክሎ ማሳደግ ሕይወትን ማስቀጠል ነው ብላለች።
በተለይ ተራራማ አካባቢዎችን በእጽዋት መሸፈን አረንጓዴ እይታን ከመፍጠር ባለፈ የጎርፍ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችልም ተናግራለች።
የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡም በቀጣይ እንክብካቤ እንደምታደርግ ገልጻለች።