የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኞችን አገልግሎት በማሻሻል ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኞችን አገልግሎት በማሻሻል ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ውድድር አሸንፎ ለመውጣት የደንበኞችን አገልግሎት በማሻሻልና በትብብር አየር መንገዶችን በማቋቋም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱን በ2024/25 ወይም በ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው በመግለጫቸው፤ ዓመቱ በዓለም የተለያዩ አገሮች የተከሰቱ ጦርነቶች፣ የዓለም ኢኮኖሚ በ2024 ዓመት ከነበረበት እድገት መቀዛቀዝ እንዲሁም ሌሎች ክስተቶች ተጨምረው ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉን የፈተኑ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ በዓለም ላይ አምስት ቢሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ እንደተቻለ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከ19 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ማጓጓዙን አብራርተዋል።
ከእነዚህ መካከል 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን የዓለም አቀፍ ተጓዦች እንዲሁም ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የአገር ውስጥ መንገደኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ 785 ሺህ 323 ቶን ጭነት በማጓጓዝ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአራት በመቶ እድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ከአምናው የስምንት በመቶ እድገት ያለው ገቢ መገኘቱን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገት የሚል ስትራቴጂ በመከተል ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ወደ ዋርሶ፣ ሞኖሮቢያ፣ ፖርት ሱዳን፣ ሻርጂያ፣ ዳካና ሀይድራባድ ከተሞች ስድስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን ማስፋት መቻሉን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸናፊነቱን ለማስቀጠል 1 ሺህ 500 በላይ ኢትዮጵያውያን የአቬሽን ባለሙያዎችን ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደንበኞች አገልግሎትን ለማሻሻልና የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት በሚችል መንገድ የማስፋፊያ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የደንበኞች አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ በጥናት ላይ ተመስርቶ በዚህ ዓመት ወደ ትግበራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከዚህም ባለፈ ለአውሮፕላን ጥገና የሚውሉ ዘመናዊ የጥገና ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የተለያዩ አየር መንገዶችን በትብብር ሲያቋቁም እንደነበር አስታውሰው፤ በሎሜ ቶጎ፣ ማላዊና ዛምቢያ ያቋቋማቸው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የአውሮፕላን ጣቢያ ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አስታውሰው፤ ተነሺ አርሶ አደሮች የሚሰፍሩበትና ዘላቂ ሥራ የሚሰሩበት ከባቢ ግንባታ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡