በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የአንድ ሀገር የመልማት እና የማደግ ፍላጎት ሊገደብ አይገባም - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የአንድን ሀገር የመልማት እና የማደግ መብት በፍጹም መወሰን የለበትም ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ ዛሬ በተርኪሚኒስታን መካሄድ ጀምሯል።


 

በኮንፍረንሱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ፣እስያ፣አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 32 ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል።

ከተሳታፊዎቹ ሀገራት መካከል 16 ከአፍሪካ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኮንፍረንሱ ላይ ባደረጉት ንግግር የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ያሉባቸውን የልማት፣የኢኮኖሚ እና የእድገት ፈተናዎችን አንስተዋል።

በማደግ ላይ የሚገኙ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የመልማት አቅማቸው ባሉበት መልክዐ ምድራዊ ስፍራ ምክንያት ሊገደብ እንደማይገባ አመልክተዋል።

ዋና ፀሐፊው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የዓለምን ሰባት በመቶ ህዝብ የያዙ ቢሆንም በዓለም ኢኮኖሚና ንግድ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከአንድ ፐርሰንት ጥቂት ሻገር ያለ መሆኑን ገልጸው ይህ ትልቅ ኢ-ፍትሃዊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሀገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም የጉዳቱ ዋንኛ ሰለባ መሆናቸውን አንስተዋል።

የዓለም ማህበረሰብ ሀገራቱ በዓለም ኢኮኖሚ እና የንግድ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ድርሻ እንዲያድግ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።


 

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም የንግድ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲጨምር የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ያሻል ያሉት ዋና ፀሐፊው፥ ይህም ሀገራት ጥሬ ምርቶችን ከመላክ ከፍተኛ እሴት ያለው ምርት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያደርጋል ነው ያሉት።

የባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት አነስተኛ ወለድ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ለሀገራት ተደራሽ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከትስስር ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን የመሰረተ ልማት እና መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህም ድንበር ተሻጋሪ አሰራሮችን ማቅለል፣የተለያዩ የመመዘኛ ደረጃዎችን ማጣጣም እንዲሁም የተሳለጠ ንግድና ትራንዚት እንዲኖር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት።

ጉቴሬዝ በመሰረተ ልማት መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይገባል ያሉ ሲሆን የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የማይበገር የትራንስፖርት መተላለፊያ መስመር፣ ድንበር ተሻጋሪ የእርስ በእርስ የኢነርጂ ትስስር፣ ሰፊ የአየር ትስስር እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የሎጅስቲክስ አውታሮች እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል።

ሀገራቱ ያለባቸውን የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እክሎች ምላሽ ለመስጠት ፍትሃዊ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፈን እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

ኮንፈረንሱ ላይ ኢትዮጵያ እና የባህር በር የሌላቸው ሌሎች ሀገራት በዓለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በትስስር፣ በፍትሃዊ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲያድግ ግፊት እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።

ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም