በክልሉ ቡናን በጥራትና በብዛት አዘጋጅቶ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ቡናን በጥራትና በብዛት አዘጋጅቶ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው

ዲላ ፤ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ቡናን በጥራት እና በብዛት አዘጋጅቶ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ቡና እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር በቡና የእሴት ሰንሰለት ዙሪያ የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ አካሂዷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳሉት ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ42 ሺህ 900 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል።
የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ለቡናው ጥራት የተሰጠው ትኩረት ለውጤታማነቱ የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ይህንን ተግባር የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል በተያዘው ዓመት ቡናን በጥራትና በብዛት በማዘጋጀት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ የሆነውን የይርጋጨፌ ቡና በጥራትና በብዛት ለገበያ ለማቅረብ መታቀዱን አመልክተዋል።
የቡና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የግብይት ስርዓቱን ለማዘመን ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አቦሴ ናቸው።
በዚህም በቡና እሴት ሰንስለት ውስጥ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት የተሻለ የምርት አቅርቦት ለመፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ማቅረብ እንዲችል አቅሙን ማዳበር እንደሚገባ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ለዚህም በ18 ቡና አብቃይ አካባቢዎች ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቅስዋል።
የጌዴኦ ዞን ቡና ላኪዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ወራሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ ለቡና ጥራት የተሰጠው ልዩ ትኩረት አርሶ አደሩንና ላኪውን ተጠቃሚ ያደረገ ነው።
በተያዘው ዓመት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉና የዞኑ የዘርፉ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር አባላት፣ ቡና ላኪ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች እንዲሁም አቅራቢዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።