ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋን በራስ አቅም ለመቋቋም የቡሳ ጎኖፋ ስርዓት የበለጠ መጠናከር አለበት

ባሌ ሮቤ ፤ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋን በራስ አቅም ለመደጋገፍ የተቋቋመው ቡሳ ጎኖፋ ስርዓት የበለጠ እንዲጠናከር የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ  እንዲጠናከር ተጠየቀ። 

የቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳትና ሀብት የማሰባሰብ ስራን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መድረክ በባሌ ሮቤ ተካሂዷል።


  

በኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወርቅነህ ኃይሌ እንደገለፁት፥ ቡሳ ጎኖፋ  የኦሮሞ ህዝብ የቀደመ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልን ማጎልበት ያለመ ነው።  

በዚህም ህዝቡ የነበረውን የመረዳዳት ባህል በማጠናከር በራስ አቅም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም በተሰራው ስራ አበረታች ለውጦች መታየታቸውን አንስተዋል።

በተለይ ባለፈው በጀት ዓመት በተከናወኑ ስራዎች ከ106 ሚሊዮን የሚበልጥ ብር ከአባላቱ መዋጮና በስጦታ መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

ለትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር በተሰበሰበው የምግብ እህል ከ97 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች  መመገብ መቻሉን አክለዋል።

የባሌ ዞን የቡሳ ጎኖፋ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በሺር በከር በበኩላቸው በዞኑ በቡሳ ጎኖፋ ስርዓት ከ800 ሺህ በላይ አባላት ማፍራት መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ስራውን አጠናክሮ ለመቀጠል መድረኩ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።


 

በአዲሱ የበጀት ዓመትም የአባላቱን ቁጥር ከ800 ሺህ ወደ 820 ሺህ በማሳደግ ከአባላቱ የሚሰበሰበውን መዋጮና ስጦታ ወደ 193 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዞኑ አመራርና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል። 

በተለይ ተጨማሪ አባላትን በማፍራት፤ በጥሬ ገንዘብና በአይነት እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ይበልጥ በማሳደግ በዞኑ የሚገኙ የተቸገሩ ዜጎችን በራስ አቅም የመደገፉ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም እያመጣ የሚገኘው ለውጥ የሚበረታታ በመሆኑ ዘርፉን ለማጠናከር የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም