የተከልነውን ችግኝ ተንከባክበን እናሳድጋለን - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የተከልነውን ችግኝ ተንከባክበን እናሳድጋለን - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች

ደብረብርሃን፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፡- በደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ አረንጓዴ ዐሻራቸውን ለማኖር የተከሉትን ችግኝ ተንከባክበው እንደሚያሳድጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ሰራተኞች ገለጹ።
የዲስትሪክቱ ሰራተኞች መርሃ ግብሩን ያከናወኑት "በመትከል ማንሰራራት"በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ልመነው መንግስቱ፤ የደብረብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ዞን ምርታማነት ይበልጥ እንዲያድግ ድጋፋቸውን ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማኖር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ አሳድገው ለውጤት እንደሚያበቁም ተናግረዋል።
ሌላው የዲስትሪክቱ ሰራተኛ ጳውሎስ አረጋዊ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለድህነት ቅነሳው ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለማሳደግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረብርሃን ዲስትሪክት ዋና ዳይሬክተር ሮቤል ጨበር እንዳሉት፤ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን እየተከናወኑ ባሉ የልማት ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ነው።
አንዱ የልማት ተሳትፏቸው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ደብረብርሃንን ጨምሮ በሸዋሮቢት ፤ ዓለም እና በሬማ ከተሞች ከ15ሺህ በላይ ቸግኝ ለመትከል አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የደብረብርሃን ከተማ የኮሪደር ልማትን ለመደገፍ ዲስትሪክቱ አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።