በክልሉ የውሃ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በተደረገ ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የውሃ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በተደረገ ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው

አዳማ ፤ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የውኃ አገልግሎት ተቋማት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ በተደረገ ጥረት ውጤት እየተገኘ መምጣቱን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው የክልሉ የውሃ አገልግሎት ተቋማትን አሰራር ከማዘመንና ጥራት ያለውን አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ስራዎችና የአዲሱ በጀት ዓመት የዘርፉ ዕቅድ ላይ በአዳማ ከተማ እየመከረ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ለማሻሻልና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋማቱ አሰራራቸውን በማዘመን የተገልጋዩን እርካታ እንዲያሳድጉ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንኪኪ ነፃ በማድረግ ዘርፉ የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ፣ የውሃ ምርታማነትን መጨመርና ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ጥሩ ጅምሮች እንዳሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ካሉት 235 የውሃ አገልግሎት ተቋማት ውስጥ በከተሞች የሚገኙት 95 ተቋማት ዲጂታል አገልግሎትን ለህዝቡ ተደራሽ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ተቋማቱ ከመንግሥት በጀት ጥገኝነት ተላቀው በወጪ ራሳቸውን በመቻል የጥገናና የማስፋፊያ ስራን በራሳቸው አቅም ማከናወን እንዲችሉ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ነው ኢንጂነር ሚሊዮን የገለጹት።
አሰራራቸውን ዘመናዊና ዲጂታል ካደረጉት የውሃ አገልግሎት ተቋማት ውስጥ የ54 ከተሞች የውሃ ተቋማት በሚያመነጩት ገቢ ራሳቸውን በመቻል ጥገናና የማስፋፊያ ሥራዎቻቸውን በራሳቸው እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በቢሮው የመጠጥ ውሃ ተቋማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጀበል አባፊጣ በበኩላቸው በክልሉ የከተማና የገጠር የውሃ አገልግሎት ተቋማትን የማቀናጀት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም በክላስተር በማደራጀት በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በውሃ ምርት፣ በፋይናንስና አስተዳደር የተሻለ አቅም ካላቸው ጋር በማስተሳሰር አሰራራቸውን ከማዘመን ጀምሮ ልምድና ሀብት በጋራ በመጠቀም የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ መደረጉን አስረድተዋል።
በዚህም በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ176 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የመጠጥ ውሃ ማምረት እንደተቻለ ያስታወሱት አቶ ጀበል፣ አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማዘመን ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻልና ቀልጣፋ ማድረግ፣ የመጠጥ ውሃ ምርትን መጨመርና በዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በወጪ ራሳቸውን ያልቻሉ የውሃ ተቋማት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግና የተገልጋይ እርካታ ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።