በክልሉ መናኸሪያዎች የተጀመረው የ"ኤሌክትሮኒክስ " ክፍያ የአሰራር ስርዓት ለተጓዦች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መናኸሪያዎች የተጀመረው የ"ኤሌክትሮኒክስ " ክፍያ የአሰራር ስርዓት ለተጓዦች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው

ባሕርዳር፤ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተሽከርካሪ መናኸሪያዎች የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ( የኢ-ትኬት) ክፍያ የአሰራር ስርዓት ለተጓዦች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።
የክልሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ባለስልጣን አመራሮች በቀድሞ የባሕርዳር የተሽከርካሪ መናኸሪያ የተተገበረውን የመንገደኞች ኤሌክትሮኒክስ የትኬት ክፍያ ስርዓት ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ማለድ እንደገለጹት፤ በመናኸሪያዎች ውስጥ ከዚህ በፊት ጫኝ እና አውራጅ እንዲሁም ህገ ወጥ አሽከርካሪዎች በተጓዦች ላይ እንግልትና ጫና ሲያደርሱ ቆይተዋል።
ተጓዡን ለአላስፈላጊ ብዝበዛ ጭምር ሲዳርግ የቆየውን ይህንን ኋላ ቀር አሰራር ለማስወገድ በ2016 ዓ.ም በስድስት መናኸሪያዎች ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ(የኢ-ትኬት) ክፍያ ስርዓት እንደተጀመረ አውስተዋል።
በእነዚህ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመጠቀምና በማስፋት አሁን ላይ በ32 መናኸሪያዎች የኤሌክትሮኒክስ (የኢ-ትኬት) ክፍያ ስርዓት ተዘርግቶ መተግበር መቻሉን አስታውቀዋል።
ይህም ለተጓዦች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሕብረተሰቡ በሚታወቅ ተሽከርካሪ እና የታሪፍ ክፍያ ወደ ፈለገው አካባቢ በነጻነት የሚጓዝበት አሰራር ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ስርዓቱ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግና ትርፍ ለመጫን የሚሞክር አሽከርካሪ ካለ ትኬቱ ላይ በሚገኘው ስልክ ቁጥር በመደወል ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ይህም ተገልጋዮች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የቆየውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ ባለስልጣኑ በልዩ ትኩረት በመስራቱ የተገኘ ውጤት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በክልሉ 252 የተሽከርካሪ መናኸሪያዎች እንደሚገኙ ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም መናኸሪያዎች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አሰራር ስርዓት ተዘርግቶ ለመተግበር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በባሕርዳር የተሽከርካሪ መናኸሪያ ኢዜአ ያነጋገራት ተጓዥ ወጣት ሶስና ደሳለኝ በሰጠችው አስተያየት ፤ የኢ-ትኬት ስርዓቱ የተሳፋሪዎችን መብት ያስከበረና አላስፈላጊ ግፊያን ማስቀረት የቻለ ነው ብላለች።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በየመንገዱ ትርፍ እየተጫነና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ተሳፋሪው እንዲከፍል እየተደረገ እንደነበር አስታውሳ፤ አሁን ላይ ችግሩ በመቃለሉ የሚያስደስት መሆኑን ገልጻለች።