ቀጥታ፡

በክልሉ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በምርምር የታገዘ ስራ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል

ባሕርዳር ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሽታን አስቀድሞ በመከላከል የሕብረተሰቡን ጤና  አጠባበቅ በምርምር ታግዞ ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ የ2017 ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳሉት፤ በ2018 በጀት ዓመት የሕብረተሰቡን የጤና ስጋት ለመቀነስ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በቅንጅት ይሰራል።


 

የወባ በሽታና ኮሌራን ጨምሮ በሌሎችም የጤና ጠንቅ በሆኑ በሽታዎች ሕብረተሰቡ እንዳይጋልጥ አስቀድሞ ለመከላከል በተቀናጀ መንገድ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት።

በምርምር ታግዞ  የመከላከሉን ተግባር ይበልጥ ለማጠናከር  ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

ለዚህም ዘመናዊ የላቦራቶሪ መሳሪያዎችንና ግብዓቶችን ተጠቅሞ መድሀኒት የተላመዱ በሽታዎችን የመከላከል ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ለሕክምና ተቋማት  ግብዓት የማቅረቡን ተግባር በማጠናከር  የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገለጸዋል።


 

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል ውጤታማ ስራ መከናወኑን አስታውሰው፤ ሌሎችን በሽታዎች የመከላከሉ ስራም አፈጻጸም መልካም መሆኑን ተናግረዋል። 

በተያዘው የበጀት ዓመትም  ከአጋር አካላት ጋር በማስተባበር በጤና  ተቋማት የግብዓት አቅርቦቱን በማጎልበት የሕክምና አገልግሎቱን የማዘመን ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በጤናው ዘርፍ በተካሄደ ሪፎርም ጠንካራ የጤና ስርዓት በመገንባት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሃይሉ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በሪፎርሙ የሕብረተሰብ ጤና ምርመራ ጥራት ያለውና የማይበገር የላቦራቶሪ ስርዓት በመዘርጋት ጥራትና ተደራሽነትን የማጠናከር ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

ጤንነቱ የተጠበቀና የበለፀገ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያስችል የጤና ፖሊሲ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም