የአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት የነዋሪውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - አስተዳደሩ

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ በአርባ ምንጭ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የነዋሪውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እያሳለጠ መሆኑም ተመላክቷል።


 

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ገዳሙ ሻምበል ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ የነዋሪዎችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ለዚህም ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርአትን የሚያጠናክሩ በርካታ መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ከእነዚህ መካከል በከተማዋ የተገነባው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ዕድገት እንዲሳለጥ ማገዙን ጠቁመዋል።

በከተማው በሁለት ምዕራፍ 11 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንና እስካሁንም ከ8 ኪሎ ሜትር በላይ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት በማጉላት የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ከ700 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አመልክተዋል።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል በንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት ኡስማን አብዱ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እያሳለጠ መሆኑን ተናግሯል።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራቶችና መዝናኛዎች ማካተቱ የንግድ ሥራውን በተሻለ ለማከናወን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጿል።


 

የኮሪደር ልማቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት አለማየሁ ነጋ ነው።

የልማት ሥራው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራዎች እንዳያሳልፉ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግሯል።

የኮሪደር ልማቱ መንገዶችን በማስፋት ለሰዎች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ በላይ ከተማዋ ማራኪ ገጽታ እንድትላበስ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ቤዛዊት ወርቁ የተባሉ ነዋሪ ሲሆኑ ልማቱ ከንግድ ሥራ የሚያገኙት ገቢ እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም