የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የተሻለ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንዲኖረን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

‎ወልቂጤ፤  ሐምሌ 29/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የተሻለ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንዲኖረን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ በወልቂጤ ከተማ ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎች ተናገሩ።

‎‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በበኩሉ በክረምት ወራት በእረፍት ላይ ያሉ ተማሪዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ሁኔታዎች ተመቻችተው ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቋል።


 

ስልጠናውን እየተከታተሉ ካሉ ተማሪዎች መካከል በከተማው ያበሩስ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ተማሪ ኤሰትን ሲሳይ እየወሰዱት ያለው ስልጠና ዲጂታል እውቀትና ክህሎትን ለመጨበጥ እንዳስቻላቸው ተናግሯል። 

መንግስት ስልጠናውን በነጻ ማመቻቸቱንና እሱም ተጠቃሚ መሆኑን ገልጾ፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ እንዲጓዝ ታስቦ  ስልጠናው በመንግስት በመመቻቸቱ አመስግኗል። 

‎በስልጠናው እያገኘ ያለው ዲጂታል እውቀት በቀጣይነት ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ ራሱን እያሳደገ ለመምጣት መነሳሳት እንደፈጠረበት ተናግሯል። 


 

‎በወልቂጤ ከተማ ጃይካ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ከፍል ተማሪዋ ሃሮት ኪዳኔ፤ የኮደርስ ስልጠና የክረምት የእረፍት ጊዜዋን ባልተገባ ቦታ እንዳታሳልፍ ያገዛት መሆኗን ገልጻለች።

‎ስልጠናው ለቴክኖሎጂ ያላትን ቅርበት እያሳደገላት መሆኑን ጠቁማ፣ ዘመኑ ዲጂታል በመሆኑ በቴክኖሎጂ እውቀት ብቁ ሆና ለመገኘትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የስልጠናው ጠቀሜታ የጎላ ነው ብላለች።

መደበኛ ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን የኮደርስ ስልጠና በመውሰድ ራሳቸውን ለማብቃት እንዲጠቀሙበትም መክራለች።

‎ወጣቶች ጊዜው የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ እውቅት በመጨበጥ ብቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስልጠናው በተለያዩ የዞኑ ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ ናቸው።


 

‎እንደእሳቸው ገለጻ በዞኑ ከፍተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የስልጠና ማዕከላት ተዘጋጅተው ወደ ተግባር ተገብቷል።

በአሁኑ ወቅትም ከ9 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስልጠናውን የወሰዱ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ድረ ገጽ እስከማልማት መድረሳቸውንም ገልጸዋል።

‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ልማትና እና አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንዳሉት የኮደርስ ስልጠና በንቃት እየተሰጠ ነው።


 

በዲጂታል እውቀት የጎለበተ ዜጋ ለመፍጠር የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

‎የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የሰልጣኞችን የቴክኖሎጂ እውቀት በማጎልበት የፈጠራ አቅም እና ተወዳዳሪነታቸውን እያሳደገው መሆኑንም አቶ ከበደ አስታውቀዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ ‎በክልሉ በተያዘው የክረምት ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም