የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2017 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2017 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው የአየር መንገዱን እኤአ የ2024/25 ወይም የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ በጀት ዓመቱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ተፅዕኖ ያሳደረ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይም በአለም የተለያዩ ሀገራት የተከሰቱ ጦርነቶች፤ የዓለም ኢኮኖሚ ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረበት እድገት መቀዛቀዝ እንዲሁም ሌሎች ክስተቶች የአየር ትራንስፖርት ዘርፉን የፈተኑ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ በዓለም ላይ አምስት ቢሊዮን መንገደኞችን በአየር ትራንስፖርት ማስተናገድ እንደተቻለ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 19 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ማጓጓዙን አብራርተዋል።
ከዚህ ውስጥ 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ እንዲሁም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ መንገደኞች መሆናቸውን ተናግርዋል።
ከዚህም ባለፈ 785ሺህ 323 ቶን ጭነት በማጓጓዝ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአራት በመቶ እድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር 8 በመቶ እድገት ተገኝቷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገት የሚል ስትራቴጂ በመከተል ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ስድስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችን ማስፋት መቻሉን ጠቅሰዋል።