በአዲስ አበባ ድንገተኛ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ድንገተኛ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ድንገተኛ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የመዲናዋ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አህመድ መሐመድ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ አደጋን ቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
በዚህም በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴሎችና ተቋማት የቅድመ ጥንቃቄ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አደጋ ከተከሰተ በኋላም ፈጣን ምላሽ የመስጠትና በአደጋው የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ የማቋቋም ስራዎችን እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
ተቋሙ በሚሰራቸው ሰራዎች የህብረሰተቡ የግንዛቤ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ጉዳዮች ሲኖሩ ህብረተሰቡ በ939 የፈጣን ጥሪ ማቅረብ ሂደቶች መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 589 የተለያዩ አደጋዎች መከሰታቸውንና እነዚህ አደጋዎች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መከላከል መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም የድንገተኛ አደጋ መጠንን በእጅጉ መቀነስ የሚያስችሉ የግንዛቤ ፈጠራና መከላከል ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተለያዩ ዘርፎች በሰለጠነ የሰው ኃይል ታግዞ ድንገተኛ አደጋን መከላከል፣ ፈጣን ምላሽ መስጠትና በአደጋው የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማቋቋም ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛል፡፡