የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም ኮንፍረንስ በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲየም እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም ኮንፍረንስ በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲየም እየተካሄደ ነው
ሐረር፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ አራተኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሰላም ኮንፍረንስ በሁለተኛ ቀን ውሎው በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
'ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው አራተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ በሐረር ከተማ ኢማም አህመድ ስታዲየም ነው እየተካሄደ ያለው።
በኮንፍረንሱ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶችና ተወካዮች፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ታድመዋል።
እንዲሁም የየክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሃይማኖት ተቋማትና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ኮንፍረንሱ ህዝቡ ሰላሙን እንዲጠብቅና የሰላም ባለቤት ሆኖ እንዲሰራ፣ ሰላም በአገሪቷ በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶችና ምዕምናን ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በሰላም በአንድነት እና አብሮነት ፀንታ እንድትቆም ህብረተሰቡን ለማነቃቃት ያለመ ነው።
በኮንፍረንሱ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂዎች የሰላም መልዕክትና ጥሪ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አራተኛው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት የሰላም ኮንፍረንስ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ ከሐረሪ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መሆኑ ተመልክቷል።