የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት የሚያስገኝ ተግባር ነው

ድሬደዋ፤  ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ) ፡- የአረንጓዴ ዐሻራ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት የሚያስገኝ ተግባር  መሆኑ  ተገለጸ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በድሬደዋ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማኖር  የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመሩ ሲሆን፤ የልማት ስራዎችን እንቅስቃሴንም ጎብኝተዋል።


 

ላለፉት ሶስት ቀናት ሲከናወን በቆየው በዚሁ መረሃ ግብር ላይ ከፍተኛ አመራሮችና አምባሰደሮች ተሳትፈዋል። 

ተሳታፊዎቹ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያውያንን በፍቅር እና በአንድነት ለአገር ከፍታ እንዲተሙ ያስቻለ ድንቅ አገራዊ ፕሮጀክት ነው።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤  የአረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ተፅዕኖ በመቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞን እያፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ የብልጽግና ጉዞ ማስተሳሰሪያና ማሳኪያ የሆነው  የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀከት በስኬት እየተጓዘ ይገኛል ብለዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤  ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክት እያከናወነች የምትገኘው አብነታዊ ተግባር ለቀጣናውን ብሎም የአፍሪካ  ብልፅግና መሳካት መሠረታዊ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለፃ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ መትከል ጉዳይ ብቻ አይደለም፤  ፍቅርን ፣ሰላምንና አንድነትን ከመላው የቀጣናውና የአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚገነባበት አስተሳሳሪ ፕሮጀክት  ነው።

በመሆኑም የሚተከሉትን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በጥንቃቄ ተንከባክቦ ማሳደግ የሁላችንም ግዴታ ነው ሲሉም  አስገንዝበዋል ።


 

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀኔራል ባጫ ደበሌ ፤ በድሬደዋ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአመራሮችና በነዋሪዎች ውብ ቅንጅት እየተመዘገበ የሚገኘውን ውጤት በዘላቂነት ለማስቀጠል የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም