በጋምቤላ ክልል በነሐሴ ወር መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 29/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የነሐሴ ወር መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታወቀ።

በክልሉ ሊኖር የሚችለው ጠንክር ያለ የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራ ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም ቅጽበታዊ ጎርፍበመፍጠር በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ማዕከሉ አሳስቧል።

የማዕከሉ መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የክረምት ጊዜ መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በክልሉ በተለይም የነሐሴ ወር የዝናብ ስርጭት ከሌሎቹ ወራት በተለየ ሁኔታ ጠንከር ያለ እንደሚሆን ነው የገለጹት።

በክልሉ ሊኖር የሚችልው የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራ በተለይም ዘግይተው ለሚዘሩና ረጅም ጊዜ ለሚወስዱ ሰብሎች አመች መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለበጋ የግብርና ልማት ስራዎች ተጨማሪ ውሃ ለመያዝና ግድቦችን ለመሙላት አዎንታዊ ሚና እንዳለው አስገንዘበዋል።

በአንፃሩ የክልሉ መልክዓ ምዕድራዊ አቀመማጥ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአጎራባች ዞኖችና ክልሎች የሚጥለው ጠንክር ያለ ዝናብ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል ተናገረዋል።

በተለይም ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ አራት ትላልቅ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ለጎርፍ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም በወንዞች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመው ባለድርሻ አካላት ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጋምቤላ አደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በክረምቱ ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ ተጋላጭነት ለመካለከል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እያከናወነ ስለመሆኑ በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም