የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት በሐረር ከተማ ኢኮ ፓርክ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት በሐረር ከተማ ኢኮ ፓርክ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
ሐረር፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት በሐረር ከተማ ከመደመር ትውልድ መጽሀፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ በተገነባው ኢኮ ፓርክ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።
የጉባኤው አባላት የሐረር ከተማን የኮሪደር ልማትና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጨምሮ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ተወካዮች፣ ከተለያዩ ክልሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሐረሪ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የጉባዔው አባላት ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሐረርን የቱሪስት መስህብነት ለማጉላት ከፍተኛ አቅም ያለውን የኮሪደር ልማት ተመልክተዋል።
በተጨማሪም የጀጎል ግንብን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በነገው እለትም የጉባኤው አባላት በሐረር ከተማ በሚገኘው ኢማም አህመድ ስታዲየም የሰላም መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት 4ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ "ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት'' በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ እየተካሄደ መሆኑ ይታወሳል።