በምስራቅ አፍሪካ የሴቶች የታዳጊዎች የቴኒስ ውድድር ላይ አሸናፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ የሴቶች የታዳጊዎች የቴኒስ ውድድር ላይ አሸናፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ከ12 ዓመት በታች የቴኒስ ውድድር ያሸነፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዛሬ አቀባበል ተደርጎለታል።
የብሔራዊ ቡድኑ ልዑክ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በውጤታችሁ ኮርተናል፤ እንኳን ደስ አላችሁ። ከፊታችሁ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ተደጋጋሚ ድል እንዳለ ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድል ማስመዝገብ እንደሚቻል እናንተ ማሳያ ናችሁ ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ስፖርተኞቹ በድሉ ሳይዘናጉ በቀጣይ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድሎችን ለማስመዝገብ በርትተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ታምራት በቀለ በበኩላቸው ውጤቱ በዘርፉ አበረታች እና ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ፤ ተተኪ ወጣት የቴኒስ ባለተሰጥኦዎችን የሚያበረታታ እና ስፖርቱን በኢትዮጵያ የሚያሳድግ ድል እንደሆነ ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ለስፖርተኞቹ የማበረታቻ ሽልማት ለተወዳዳሪዎች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሴት ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ አሸናፊ የሆነው ታንዛንያን፣ ሲሸልስን እና ሩዋንዳን በተመሳሳይ 3 ለ 0፤ ብሩንዲ እና ኬንያን ደግሞ በተመሳሳይ 2 ለ 1 በማሸነፍ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።