ቀጥታ፡

ኢዜአ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጽናትና የአፍሪካውያንን ትርክት የመገንባት ተግባሩን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጽናት፣ የአፍሪካውያንን ትርክት የመገንባትና የማንጸባረቅ ተግባሩን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት/ኢዜአ/ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ፣ የነባር ህንጻ ዕድሳት እንዲሁም የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢዜአ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጽናትና የአፍሪካውያንን ትርክት የመገንባት ተግባሩን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

የህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማፅኛ፣ አፍሪካውያን በራሳቸው አስተሳሰብ የራሳቸውን ታሪክ እንዲናገሩ ዋነኛ የትርክት ማሰራጫ መሆን እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።

ኢዜአ አጀንዳ በመቅርጽና የሚዲያ ትርክት በመገንባት በኩል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ኢዜአ ሀገራዊ አጀንዳ የመቅርጽና የተዛቡ ትርክቶችን የመመከት ተግባሩን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት።


 

ኢዜአ የከፍታ ጉዟችን የመረጃ መሳሪያ፣ የሀገርና የአፍሪካ የተስፋ ትርክት ፈጣሪና ነጋሪ ሆኖ መቀጠሉንም ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ አንጋፋና ቁልፍ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፤ ለአህጉራችን ደግሞ የመስፈንጠሪያ ኃይሏ፣ የስኬትና አንድነቷ አብሳሪ ድምፅ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን በሁሉም ዘርፎች መሆናቸውን አንስተው፤ በዚህ በኩል ኢዜአ ያከናወናቸው ተግባራት ሰፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ለአፍሪካ መነሻ መሆኗን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋና ወጊ የሆነ ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል፡፡

ኢዜአ ብዙ የቤት ሥራ ያለበት ተቋም መሆኑን ጠቁመው፤ አጀንዳ በመቅረጽና የሚዲያ ትርክትን መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ አንጋፋ ተቋም መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን በሚዲያና በሌሎችም ዘርፎች ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው፤ ተቋሙ የጀመራቸውን የለውጥ ስራዎች በማስቀጠል የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ብሎም ለአፍሪካውያን መሸጥ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡


 

ኢዜአ በሁሉም አካባቢ ለመድረስ አድማሱን እስከ ወረዳ ማስፋቱን ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስትም የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

በኢዜአ መልካም ነገሮች ማየታቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪ ስራዎች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ማሳየት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያውያን መልካም ገጽታችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለአፍሪካውያን ወንድሞች መናገር ተገቢ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የተሳሳቱና የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል እንደ ኢዜአ ባሉ የሚዲያ ተቋማት አጀንዳ መፍጠር እና ቀድሞ ተረድቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢዜአ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደረጉ የተቋሙ የሥራ ሃላፊዎች፣ የቦርድ አመራር አባላት እና ሠራተኞችን አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም