የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያን አቋም ላለፉት ከ82 ዓመታት በላይ በማይናወጥ መልኩ ለዓለም ያስተጋባውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ን ዛሬ መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ኢዜአ ዛሬ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪካዊ ዐሻራውን በአዲስ እሳቤ እያዳበረ ለስራ ምቹ የሆነ ከባቢን፣ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ፣ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን በመገንባት የመጪው ዘመን ቀንዲል ሆኖ ለማገልገል በብዝኃ ቋንቋ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ለዓለም ለማሳየት የያዘው ግብ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ተቋሙ ሀገራዊ ጥቅሞችን እያስጠበቀ፣ የባህልና የቱሪዝም ሀብቶችን እያስተዋወቀ፣ መልካም ገፅታን ለዓለም እያሳየ ለመቀጠል በሰው ኃይልና በሚዲያ ቴክኖሎጂ ራሱን እያደራጀ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ጅምር እንደሆነም አመልክተዋል።
በተለይ በውጭ ቋንቋዎች(Pulse of Africa) የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ራሳችን ተልመን፣ ራሳችን ሰርተን፣ ራሳችን ጽፈን፣ ራሳችን ለዓለም የምንናገረውና የምናሳየው መሆን ይኖርበታልም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልክታቸው።
ለዚህ ደግሞ መንግስት ተቋሙ የጀመራቸውን ሀገራዊና አህጉራዊ የለውጥ አራማጅ ግቦች ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢዜአ ከዜና ባለፈ የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማፅኛ፣ አፍሪካውያን በራሳቸው አስተሳሰብ የራሳቸውን ታሪክ እንዲናገሩ ዋነኛ የትርክት ማሰራጫ መሰረተ ልማት ሆኖ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢዜአ ለጀመረው የለውጥ ስራ በትጋት ለሰሩና ለተባበሩ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።