በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተሰራ ነው

ድሬደዋ ፣ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፡- በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተሰራ መሆኑን የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችንና ባለሙያዎችን ማፍራቱንም አስታውቋል።
በድሬደዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የተያዘው በጀት አመት አቅጣጫ በሚመለከት እየተካሄደ ባለው መድረክ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር)፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት በርካታ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችና በክህሎታቸው የበቁ ባለሙያዎች ማፍራት ተችሏል ብለዋል።
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ እና በ'ሊደርሺፕ' የሶስተኛ ድግሪ ስልጠና መርሃ ግብር መጀመሩን ጠቁመው መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ 1 ሺህ 800 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በርካታ ዜጎችን ክህሎት መር አጫጭርና መደበኛ ስልጠናዎችን በመስጠት ፀጋዎችን ወደ ሃብት እንዲቀይሩ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ከከተሞች እና ክልሎች ጋር በመቀናጀት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤቶች ለማስመዝገብ እያከናወናቸው የሚገኙት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት ብቁና ውጤታማ አሰልጣኞችንና አመራሮች እያፈራ መሆኑን በመጥቀስ ።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ግምገማ የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በማረም ጥራትና ተደራሽነቱ የተረጋገጠ ውጤት ለማስመዝብ እንደሚያግዝ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፤
በግምገማው ላይ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።