ቀጥታ፡

ፕሮጀክቱ በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ እያሻሻለ ነው

አዳማ ፤ ሐምሌ 28/2017 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ ተግባራዊ  የሆነው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት  በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ  እያሻሻለ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በፕሮጀክቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና በተያዘው በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዳማ  እየተካሄደ ይገኛል።


 

በዚህ ወቅት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ ጋር በመቀናጀት በተመረጡ የሀገሪቱ ከተሞች  ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ  ከማሻሻል ባለፈ የከተሞችን ጽዳት፣ ውበትና የአነስተኛ መሰረተ ልማት ችግሮችን የሚያቃልል መሆኑን ጠቁመው፤  መንግስት በትኩረት ከሚያስፈጽማቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በፕሮጀክቱ በርካታ ዜጎችን ከተረጂነት በማላቀቅ አምራች ዜጋን ለማፍራት ማስቻሉን አመልክተው፤  በፕሮጀክቱ በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ  በማሻሻል ረገድ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከአለም ባንክ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያየ ጊዜ ያደረግናቸው የሥራ አፈጻጸም ግምገማዎች የሚያመለክቱትም ፕሮጀክቱ ከመነሻው ካስቀመጠው ግብ አንጻር አበረታች ውጤት የታየበት ነውም ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ  ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን 45 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት ገልጸዋል።

ይህም ላለፉት ዓመታት ከፕሮጀክቱ ጋር የቆዩና የተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች በዘላቂነት ኑሯቸው እንዲሻሻልና ከራሳቸው አልፈው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።


 

በሚኒስቴሩ የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ በበኩላቸው፤  በ11 ከተሞች የተጀመረው የከተሞች ሴፍቲኔት መርሃ ግብር አሁን ላይ በ88 ከተሞች ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የስራና የቁጠባ ባህላቸውን ከማሳደግ  በተጨማሪ የገቢ ማስገኛ መስክ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ በዚህ ዓመት ብቻ 288 ሺህ በላይ ዜጎችን በማስመረቅ ለውጤት ማብቃት መቻሉን አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሀሰን ሙህዬ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ በክልሉ በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ  ከማሻሻል በተጓዳኝ ከተሞች ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ እየተሰራ ነው።


 

በተለይ በፕሮጀክቱ በታቀፉ 18 ከተሞች ውስጥ በተደረገው እንቅስቃሴ የስራና የቁጠባ ባህል በማሻሻልና በከተማ ግብርና ሥራ በማሰማራት በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደበሎ ዱሬሳ በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ አማካኝነት በርካታ ዜጎች በአከባቢ ልማት፤ በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።


 

ፕሮጀክቱ በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ  በማሻሻል ረገድ አበርክቶው ትልቅ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ዓመት ብቻ 61 ሺህ ተጠቃሚዎች ጥሪት አፍርተው ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን አስረድተዋል።

ለስድስት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም