የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ያባዛቸውን ከ300 ሺህ በላይ ምርታማ የፍራፍሬ እና የአትክልት ችግኞች እያሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ያባዛቸውን ከ300 ሺህ በላይ ምርታማ የፍራፍሬ እና የአትክልት ችግኞች እያሰራጨ ነው

ደሴ ፤ ሐምሌ 28/2017 ( ኢዜአ) ፡- የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል " በባዮ ቴክኖሎጂ " ያባዛቸውን ከ300 ሺህ በላይ ምርታማ የፍራፍሬ እና የአትክልት ችግኞች እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ።
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ሀሰን እንድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የተሻሻሉ የፍራፍሬ እና የአትክልት ችግኞችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም ባለፉት ዓመታት ያሰራጫቸው ችግኞች ምርታማነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ከክልሉ ውጭ ጭምር ለማስፋት ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ዘንድሮው ከ300 ሺህ በላይ የሙዝ፣ የአናናስ፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የአፕልና የድንች ችግኞችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ፣ ለባለሃብቶችና ለማህበራት እያሰራጨ ለተከላ እንዲበቁ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግኞቹ በሽታን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ የሚደርሱና ምርታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 032 ቀበሌ አርሶ አደር ያሲን መሀመድ በሰጡት አስተያየት፤ ከማዕከሉ ያገኟቸው የፍራፍሬ ችግኞች በሽታን ተቋቁመው ባጭር ጊዜ የሚደርሱና ምርታማ ናቸው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ከማዕከሉ ወስደው የተከሉት የሙዝ ችግኝ በአንድ ዓመት ውስጥ ምርት በመስጠቱ ከሙዝ ሽያጭ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንና ዘንድሮም ተጨማሪ ችግኞችን መትከላቸውን ተናግረዋል።
በአርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ አስተዳደር የ07 ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ ሰይድ በበኩላቸው፤ ከማዕኩ የሚወጡ የፍራፍሬ ችግኞች ውጤታማ መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም የተከሉት የሙዝ ችግኝ ደርሶ ምርቱን ለሽያጭ በማቅረብ በዓመት እስከ 60 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዘንድሮ ችግኝ በመትከል የበለጠ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አክለዋል።
በሰኔ ወር 2011ዓ.ም ስራ የጀመረው የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት 20 ሚሊዮን የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኝ የማባዛት አቅም እንዳለው ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።