ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የሕብረተሰቡን ጤና ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተከናወኑ ነው - ኢንስቲትዩቱ

ባሕርዳር፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የሕብረተሰቡን ጤና ማሻሻል የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬከተር መሳይ ሃይሉ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ በሽታዎችን በመለየትና አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ውጤታማ ሰራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል።

ወቅታዊና ፈጣን የሆኑ የመረጃ ልውውጥና ትንተና በመስጠትም በሕብረተሰቡ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር አደጋ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን የመከላከል ስራ በልዩ ትኩረትና ቅንጅት መከናወኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የተዋስህያን ተለዋዋጭ ባህሪን ታሳቢ ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የላቦራቶሪ ውጤቶችን ጥራት የሚያረጋግጡ ስራዎች መቀጠላቸውን አመልክተዋል።

እነዚህን ጨምሮ በሀገሪቱ የሕብረተሰቡን ጤና ማሻሻል የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በበኩላቸው፤ የሕብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የላቦራቶሪ ጥራትን በማሻሻል፣ የጤና ምርምር በማካሄድ፣ የጤናና ጤና ነክ መረጃዎችን በመተንተን በትኩረት መሰራቱን አውስተዋል።

የወባና ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችሉ ሰራዎችን በማከናወን ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከልና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት በ2018 የስራ ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

እስከ ነገ በሚቆየው መድረክ የፌደራልና የክልሉ የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም