ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ለምትተገብረው ስትራቴጂ ውጤታማነት ትብብሩ ይጠናከራል - የዓለም ጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተገበረችው ለሚገኘው ስትራቴጂ ውጤታማነት ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኦውን ካሉዋ አሱመስ(Owen Kaluwa Assumes) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ስርዓትን ለማሻሻል እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

የጤናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ የታካሚዎች ደህንነትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተገበረቻቸው የሚገኙ መርሃ ግብሮችን አንስተዋል።

እኤአ በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ተግባራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰሩ ከሚገኙ ሀገሮች እንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ የዓለም ጤና ድርጅት በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግርዋል።

አራተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት በኢኖቬሽን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ሌሎች ዘርፎች የመጣውን ዕድል በጤናው ዘርፍ ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ እያደረገቻቸው የሚገኙ ስትራቴጂዎችን በመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ የሚደረጉ የኢኖቬሽን ውጤቶችን ለማስፋትና በህብረተሰብ ጤና ላይ ለሚተገበሩ ስትራቴጂዎች በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ኢኖቬሽን በጤናው ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ፣ ተደራሽነትን ለማስፋትና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በመሆኑም ትብብርን ማጠናከር፣ ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ የኢኖቬሽን ውጤቶችን መለየትና ጥቅም ላይ ማዋል ለጤና ጥራትና ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት አጋዥ እንደሆኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም