ቀጥታ፡

በኩታ ገጠም ከሚለማው የጤፍ እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት አቅደናል -አርሶ አደሮች

አምቦ፤ ሐምሌ 28/2017(ኢዜአ)፦- በመኸር አዝመራ በኩታ ገጠም ከሚያለሙት የጤፍ እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ነው።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደሮች በምርት ዘመኑ በኩታ ገጠም ተደራጅተው የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎችን እያከናወኑ ነው።

በተለይም ዘንድሮ በልዩ ሁኔታ የጀመሩት ጤፍን በኩታ ገጠም የማልማት ስራ የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያግዛቸው ተስፋ አድርገዋል።

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል የኮልባ አንጫብ ቀበሌ አርሶ አደር አሰፋ ኩመላ እንዳሉት፤ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ከሙያ ጀምሮ የተለያየ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።


 

የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ከዚህ በፊት ከሚቀርበው በተሻለ ዘንድሮ እንደቀረበላቸው ገልጸው እያለሙት ከሚገኙት የጤፍ ሰብል የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ሌላኛው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ኡማ ሳርቤሳ፤  ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማት መጀመራቸውን ገልጸው ተባብሮ መስራት የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚያግዛቸው በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

ከዚህ ቀደም በተናጥል ሲያርሱ ከአንድ ሄክታር መሬት አስከ 20 ኩንታል የጤፍ ምርት እንደሚያገኙ የተናገሩት አርሶ አደሩ ዘንድሮ በኩታ ገጠም ያለሙት እርሻ ከሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ አድርገዋል።

የኩታ ገጠም እርሻ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ጊዜን እና ጉልበትን ለመቆጠብ የሚያግዝ በመሆኑ በልማቱ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ሙሉነህ ተሬሳ ናቸው።


 

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዋዬሳ አለሙ በበኩላቸው በወረዳው የመኸር እርሻው ከግብአት አቅርቦት ጀምሮ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት 2 ሺህ 225 ሄክታር መሬት በጤፍ ሰብል ብቻ ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 2ሺህ 500 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 


 

በአጠቃላይ በወረዳው 33 ሺህ 896 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 33 ሺህ 158 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስረድተዋል።

በወረዳው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ከማዋል ባለፈ ለኩታ ገጠም እርሻ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲሳ ሀይሉ፣ በዞኑ በመኸር አዝመራው 886 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደትም ከ889 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸው የዘንድሮው መኸር እርሻ ከእቅድ በላይ መፈጸም የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ዘንድሮ  ስንዴ፣ ጤፍ እና ገብስ የመሳሰሉ ሰብሎች በኩታ ገጠም በስፋት እየለሙ መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ 91 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በጤፍ ሰብል እየለማ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም