የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ያለፈውን በታሪክነት የያዘ፤ የሚመጣውን አሻግሮ ያለመ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ያለፈውን በታሪክነት የያዘ፤ የሚመጣውን አሻግሮ ያለመ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2017(ኢዜአ)፦ የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ያለፈውን ጊዜ በታሪክነት የያዘ፤ የሚመጣውን አሻግሮ ያለመ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ፣ የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽንና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ከብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን አዲሱንና ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ ተሠርቶ የተጠናቀቀውን ኮሪደር ዛሬ ጠዋት መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ይኽ አስደናቂ ለውጥ ከተካሄደባቸው የከተማችን ክፍሎች አንዱ ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ትንሳኤ ያበሰረ ነው፡፡
ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ሳቢ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ የተከናወነው የኮርደር ልማት ስራም ድንቅ እና አዲስ አበባ እንደ ስሟ እያበበች ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ዜጎችን ለመጪው ዓለም የማዘጋጀት ተልዕኮ ማንገቡን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኤግዚቢሽኑ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ምላሽ፣ በግብርና፣ በውኃ ኃይልና ኢነርጂ እንዲሁም አቪየሽንና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ዐውደ ርዕይ መያዙንም ገልጸዋል፡፡
ወጣቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፈጠራ ስራን እንዲያጎለብት የሚያነሳሳና ትውልዱ ለሚመጣው ተግባር ራሱን የሚያዘጋጅበት ዘመኑን የዋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን አቀናጅቶ የያዘና አገልግሎትን ለተገልጋዩ መስጠት የሚያስችል ትልቅ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።