በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 27/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ አምባሳደሮችና ሠራተኞች ትላንትና በድሬዳዋ አረንጓዴ ዐሻራቸውን ያስቀመጡ ሲሆን የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎችንም አከናውነዋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በዛሬው ዕለትም በድሬዳዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙት ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የበለጸገች ሀገር መገንባት እንደሚቻል ማሳያ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በተለይም በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ድሬዳዋን ውብ የስራና የመኖሪያ ስፍራ እንዳደረጋት ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው የልማት ሥራዎቹ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መደላድል የሚፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶች በተለይም የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ይመሰክራሉ ብለዋል።
የፌዴራል ተቋማቱም ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወርደው ልማቱን ማገዛቸው ይበልጥ ብርታት እንደሚሆናቸው አንስተዋል።
የስራ ሀላፊዎቹ ከጎበኟቸው ልማቶች መካከል፣ የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የኮሪደር ልማት፣ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል፣ የገጠር ሴት ተማሪዎች መኖሪያ ተጠቃሽ ናቸው።