በአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ ተተኪዎችን ለማፍራት እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ ተተኪዎችን ለማፍራት እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ

ወልቂጤ፤ ሐምሌ 27/2017(ኢዜአ)፦ በአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ ተተኪዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ስለሺ ስህን ተናገረ።
5ኛው የኬሮድ ሀገራዊ የጎዳና ላይ የ15 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በውድድሩ ከ25 ሺህ በላይ የከተማው ነዋሪዎች እና ከ2ሺህ በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ስለሺ ስህን በዚህ ወቅት እንደገለጸው፣ አትሌቲክስ ከውድድር ባለፈ የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት ለማጠናከር ያግዛል።
ተተኪ ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጾ፣ ፌዴሬሽኑ በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ የሚያካሂደው የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በርካታ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያስቻለ ነው።
ውድድሩ በተከታታይ ለአምስት ዓመታት መካሄዱን አስታውሰው፣ ለከተማዋ እድገት እና መነቃቃት እንዲሁም የህዝብ ትስስር ከመፍጠር አንጻር የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ስፖርት ለሃገር አንድነትና ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ውድድሩ ከአብሮነት ጋር ለአምስት ዓመታት መከናወኑን የገለጸው ደግሞ የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ፕሬዚዳንት አትሌት ተሰማ አብሽሮ ነው።
ውድድሩ እንደ ሀገር ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እያስቻለ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት በወልቂጤ ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊ እሴትን ለማጎልበትና ወንደማማችነትንና አህትማማችነትን ለማጠናከር አግዟል።
ስፖርት የህብረተሰቡን አንድነትና ትበብር በማጠናከር አእምሯዊ እና አካላዊ ብቃትን ለማጎልበት ካለው ፋይዳ ባለፈ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ለማነቃቃት እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ በወንዶች 1ኛ ሐጎስ እዮጋረድ ከዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብ እንዲሁም በሴቶች ጉተኒ ሻንቆ ከኦሮሚያ ፖሊስ አንደኛ በመውጣት እያንዳንዳቸው 125ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሁለቱም ጾታዎች ሁለተኛ የወጡት 50ሺህ እንዲሁም ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ላጠናቀቁት 25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።