በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያዎች መስፋፋት ጤናችንን እንድንጠብቅ አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያዎች መስፋፋት ጤናችንን እንድንጠብቅ አስችሎናል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት በአቅራቢያችን አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ስፖርታዊ ብቃትን እንድናሻሽልና ጤናችንን እንድንጠብቅ አስችሎናል ሲሉ የጤና ቡድን ስፖርተኞች ተናገሩ፡፡
አዕምሮው የዳበረ፣ አካሉ የጠነከረ እና በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ አምራች ትውልድ ለመገንባት እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቁልፍ ሚና አላቸው።
በዚህ ሃሳብ መነሻነት በመዲናዋ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡
ኢዜአ በመዲናዋ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ባደረገው ቅኝት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኛቸውን የጤና ቡድን አባላትን አነጋግሯል።
በካዛንችዝ አካባቢ በተለምዶው 28 ሜዳ እየተባለ በሚጠራው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ብርሃኑ ሳህሉ፤ ከለውጡ ወዲህ በመዲናዋ ለነዋሪዎች በቅርብ ርቀት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደግሞ ከህጻን እስከ አዋቂ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉና ምቹ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ይህ ደግሞ በስፖርቱ ዘርፍ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እና ከተለያዩ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሳችንን እንድንጠብቅ አስችሎናል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ለስፖርት መሰረተ ልማት የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ፥ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ረዥም ዓመታትን እንዲያገለግሉ የስፖርት ማህበረሰቡ በአግባቡ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በቀበና አካባቢ በተለምዶ 15 ሜዳ እየተባለ በሚጠራው የማዘውተሪያ ስፍራ ስፖርት ሲሰራ ያገኘነው ምኒልክ ግርማ በበኩሉ፤ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ በፈለግነው ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ልምምድ እንድናደርግ ትልቅ እድል ፈጥረዋል ነው ያለው።
መንግሥት በሰጠው ትኩረት በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ለሀገር የእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ከዚህ በፊት እኛ አዋቂዎችም ሆንን ታዳጊዎች ጉዳትን በመፍራት ወደዚህ ሜዳ አንመጣም ነበር ያሉው ደግሞ አራት ኪሎ አካባቢ በተለምዶ አስር ሜዳ እየተባለ በሚጠራው እግር ኳስ ሲጫወት ያገኘነው በአምላክ ተሾመ ነው፡፡
አሁን ላይ ሜዳው በአርቲፊሻል ሳር የተዘጋጀ በመሆኑ ለአካላዊ ጉዳት የማይዳርግ እንዲሁም ዘውትር እንቅስቃሴ በማድረግ የእረፍት ጊዜያችንን ጤናችንን ለመጠበቅ እንድንጠቀምበት አድርጎናል ብሏል።