ቀጥታ፡

የቱሪዝም ዘርፉን የሃብት ምንጭነት ማጎልበት ይገባል

ዲላ ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ) :- የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅ እና በመንከባከብ በብዝሃ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የኢፌዴሪ ፕላን ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ጉብኝትና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደዋል።


 

የፕላን ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ በወቅቱ እንዳሉት የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ተፈጥሮን፣ መስህቦችንና ሰውን አስማምቶ የያዘ የቱሪዝም ሃብት ነው። 

በተለይ የአካባቢው ጥምር ግብርና ባህል የማህበረሰቡ የምግብ ዋስትና መሰረት ከመሆን ባለፈም የልዩ ጣዕም ቡና መገኛ ጭምር መሆኑን አንስተዋል።


 

የችግኝ ተከላ በማከናወን የአካባቢ ጥበቃ ባህሉ እንዲጎለበት ለሚደረገው ጥረት መጠናከር አሻራቸውን እንዳሳረፉም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች መገኛ ሀገር መሆኗን ገልፀው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን ጨምሮ የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅና በመንከባከብ የብዝሃ ኢኮኖሚ ተሳትፎአቸውን ማጎልበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ የመስህብ ስፍራ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በዚህ ስፍራ አረንጓዴ አሻራን ማሳረፍ የደን ሽፋንን በማሳደግ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመገንባት ባለፈ ቅርሱን መንከባከብ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በመጠቀም የገቢ አቅምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በተለይ አረንጓዴ አሻራን ከባህላዊ የአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር በተከናወነ ተግባር የቡና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የፕላን ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሲዳማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎችና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም