የጎፋ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገዠ ትርክትን የሚያጠናክር ስራ ላይ ማተኮር አለበት-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የጎፋ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገዠ ትርክትን የሚያጠናክር ስራ ላይ ማተኮር አለበት-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/2017(ኢዜአ)፦የጎፋ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገዠ ትርክትን የሚያጠናክር ስራ ላይ ማተኮር እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የጎፋ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የጎፋ ማህበረሰብ ቴሌቭዥን ጣቢያ ስራ እንዲጀምር የተደረገው ጥረት ተሳክቷል።
የማህበረሰብ ቴሌቭዥን ጣቢያው መቋቋሙ ለዞኑ ለክልሉ እንዲሁም ለአገር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የማህበረሰብ ቴሌቭዥን ጣቢያው በኢትየጵያ የተጀመረውን የብልጽግና ስራዎች ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበት አስታውቀዋል።
ገዠ ትርክትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡
የአካባቢውን እሴቶች በማስተዋወቅ አካባቢው የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ለአገር ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዘመን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ትልቅ መሆኑን አንስተው፤ በዞኑ የቴሌቭዥን ጣቢያ መጀመሩ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለቴሌቭዥን ጣቢያው ውጤታማነት ባለስልጣኑ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡