በክልሉ በግብርና ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግብርና ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል - ቢሮው
ቡታጅራ ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ) :-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል ክልላዊ አማካሪ ምክር ቤት ዛሬ ተቋቁሟል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በወቅቱ እንዳሉት መንግሥት ግብርናን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም በክልሉ ተቀርፀው እየተተገበሩ በሚገኙ ኢንሼቲቮች የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ጀምሮ በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ከድህነት የመውጫ መንገድ ለማድረግ በተሰራው ስራ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ጀምሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡንም ጠቁመዋል።
ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት እውን ለማድረግ ባለድርሻ አካላትን ማዕከል ያደረገ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ የላቀ ስኬት ለማምጣት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ከቢሮው ጋር በአጋርነት እየሰራ ያለው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተሾመ ይትባረክ (ዶ/ር) እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በአካባቢው የተጎዳ መሬትን የማከም፣ የእንሰት ዝርያዎችን ከበሽታ የመከላከልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ የጥናትና ምርምር ስራን ተግባራዊ በማድረግ እያገዘ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነታቸው እንዲጎለብት እየተደረገላቸው ያለው የባለሙያ እገዛ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ በመድረኩ የተገኙት ሞዴል አርሶ አደር በየነ ሀንዲሶ ናቸው፡፡
በቀጣይም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ለመትረፍ ተግተው እንደሚሰሩ ጠቁመው የግብርና ልማት አማካሪ ምክር ቤት መመስረቱ ልምድና ተሞክሮን ለማግኘት እንደሚረዳም አመልክተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይም የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አመራሮች፣ በክልሉ የሚገኙ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች፣ የምርምር ተቋማትና ሞዴል አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡