ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሃገራችን ብቻም ሳይሆን ለቀጣናው የመልማት ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሃገራችን ብቻም ሳይሆን ለቀጣናው የመልማት ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው
ሀዋሳ፤ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ):-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሃገራችን ብቻም ሳይሆን ለቀጣናው የመልማት ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ ፕሮጀክት መሆኑ ተመላከተ፡፡
የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቅርቡ እንደሚመረቅ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያውያን የትብብርና ትስስር ማሳያ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለሃገራችን ብቻም ሳይሆን ለቀጣናው የመልማት ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተማራማሪ በዓሉ ጡቄላ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ትስስርና አንድነት ጎልቶ የታየበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ ኃይል በማመንጨት የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጉልህ በመሆኑ እንደሃገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም የሀገሪቱን ገጽታ የገነባ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፥ ለሃገርም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያጎናፅፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
መንግስት እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ለአገልግሎት ማብቃቱ ልማት እንዲፋጠን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአይቻልም መንፈስን የሰበረና በአንድነት ከቆምን እንደምንችል ያሳየንበት ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃና የህዝብ ጠንካራ ተሳትፎ ወደ መጠናቀቅ መምጣቱ ሌሎች ልማቶችን በጋራ ልናሳካ እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን ዜጎች ትስስርና አንድነት ከማጠናከር ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን አብሮ የማደግና የመልማት ግብን የሚያሳካ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡