ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በድሬዳዋ ከተማ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ቤቶችን ሊገነቡ ነው

ድሬደዋ ፣ ሐምሌ 26/2017(ኢዜአ)- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በድሬደዋ የ20 አቅመ ደካማ ቤተሰቦችን ቤቶች ለመገንባት ነው የመሠረት ድንጋይ ዛሬ ያስቀመጡት።


 

በወቅቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃዳራ አበራ እንዳሉት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የአቅመ ደካማ ወገኖችን ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝተዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተቀናጀ መንገድ የመፍታት ስራ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

''በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወደቀን ማንሳት፣ የተቸገረን መርዳት፣ የህሊናና የአካል ሰላም የሚሰጥ ተግባርን መፈፀም ባህል መሆን ያለበት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተጣለላቸው ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።


 

ቤቶቹ የሚገነቡበት አካባቢም በቀጣይ "የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መንደር " በሚል ስያሜ እንደሚጠራም አመልክተዋል።

የፌደራል ተቋማት በድሬዳዋ ተገኝተው የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ለማቃለል እያከናወኑ የሚገኙት ተግባራት አበረታች ናቸው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ዛሬ በድሬዳዋ ተገኝተው ያከናወኗቸው የበጎ ፈቃድ ስራዎች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በዘንድሮ ክረምትም በአስተዳደሩ ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ከንቲባ ከድር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም