ቀጥታ፡

የስፖርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሳይንሳዊ የስልጠና ስነ-ዘዴን በመከተል የሙያተኞችን ዕውቀትና ክህሎት ማሳደግ ይገባል

አሰላ ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ) :-የስፖርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሳይንሳዊ የስልጠና ስነ-ዘዴን በመከተል የሙያተኞችን ዕውቀትና ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ለተወጣጡ የስፖርት ዘርፍ ሙያተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናን በአሰላ ጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ማስልጠኛ ማዕከል እየሰጠ ይገኛል።

የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በወቅቱ እንደገለፁት ጥራት ያላቸው ስፖርተኞችን በብዛት ለማፍራት ሳይንሳዊ የስልጠና ስነ-ዘዴን በመከተል የሙያተኞችን ዕውቀትና ክህሎትን ማሳደግ ይገባል። 


 

ይህን ለማሳካትም የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች በሳይንሳዊ ስልጠና ስፖርተኞችን ማብቃት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ስልጠናውም  የስፖርተኞችን ስነ-ልቦና፣ ስነ-ምግባር፣ ቴክኒክና ታክቲክን  ያካተተ መሆን አንዳለበትም አክለዋል።

በስፖርት ዘርፉ ሀገሪቱ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ በየደረጃው ያሉ የስፖርት ማዕከላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።


 

የአዲስ አበባ እና አሰላ ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ስፖርተኞችን አሰልጥነው በማብቃት ረገድ የተሻለ ስራ መስራታቸውን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የትምህርት ስልጠናና ውድድር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ በላይ ናቸው ።


 

በዘጠኝ የውድድር አይነቶች ስፖርተኞችን ከመመልመል ጀምሮ፣ በትጥቅ፣ በአመጋገብ፣ በህክምናና በአስተዳደር ረገድ ያሉ የአቅም ክፍተቶችን በጥናት በመለየት ምላሽ መሰጠቱን ተናግረዋል ።

በተለይ የአትሌቲክስ፣ የእግር ኳስ፣ የቮሊቦልና ቅርጫት ኳስን ጨምሮ አምስት የስፖርት አይነቶችን ያካተተ 11 ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም አቶ ደሳለኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም