ቀጥታ፡

የወልቂጤ ከተማን ለስራና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ወልቂጤ ፤ ሐምሌ 26/2017 (ኢዜአ) :- የወልቂጤ ከተማን ለስራና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ  ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

‎የከተማው ማህበረሰብ እና ታዋቂ የአትሌቲክስ ስፖርት አባላት በከተማዋ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

‎በመርሀ ግብሩ ላይም የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንዳሉት የወልቂጤ ከተማን ለስራ፣ ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በዚህም ‎የከተማዋ ነዋሪዎችን በማሳተፍ በፅዳትና ውበት እንዲሁም በሌሎች የልማት ስራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል። 


 

በስነ-ስርዓቱ ላይ ከተሳተፉት ‎አትሌቶች መካከል ኮማንደር ሰለሞን ባረጋ ከተማዋን ንጹህና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የበኩሉን ለማበርከት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።


 

የከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ የፅዳትና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲሁም  ''የጽዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ ህብረተሰቡን በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደጉን ገልጿል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የረጅም ርቀት ሩጫ አሰልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ በበኩላቸው ንፁህ አየርን ከአትሌቲክስ ስፖርት ለይቶ መመልከት ባለመቻሉ  ለተግባራዊነቱ  ፅዱ አካባቢን  መፍጠር  እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

በከተማው በተካሄደው ፅዳት ላይ ከህብረተሰቡ  ጋር በመሳተፍ  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን  የተናገረው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አማኑኤል ንጉሴ ነው።


 

ከከተማዋ ‎ፅዳት ስራ ባለፈ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል።

በመርሀ ግብሩ  ላይም የከተማው አመራሮች፣ ወጣቶች እንዲሁም አትሌቶች እና አሰልጣኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም