ቀጥታ፡

ተልዕኳችንን የኢትዮጵያን መሻት በማሳካት መለካት አለብን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን መሻት በማሳካት ተልዕኳችንን መለካት አለብን ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራር አባላትና ሠራተኞች በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካሒደዋል።


 

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ ተልዕኮውን ለማሳካት ከሚያከናውነው ተግባር በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛል።

በዛሬው እለት የተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።

አረንጓዴ አሻራ በምግብ ራስን የመቻል ጥረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን በምግብ ራስን መቻል፣ በአህጉር ደረጃ ተጠቃሽና ምቹ አገር በመፍጠር ሒደት ውስጥ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑም አክለዋል።

የተቋሙ ግብ የኢትዮጵያን መሻት ማሳካት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በዚህ ሒደት ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባር እያከናወነ የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ብልጽግና እውን ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተጨማሪም ሃምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሔደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጰያ 714 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ መቻሉን አስታውሰዋል።

በዕለቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በመትከል ማንሰራራት የሚለው አገራዊ እሳቤ ግቡን እንዲያሳካ ጥረት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

ይህን ታሪካዊ ኹነት ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ሰፊ ሽፋን ሰጥተው መዘገባቸውን ጠቁመው፤ ከችግኝ ተከላው ባሻገር ያለውን ገጽታ በመዳሰስ ጭምር ሽፋን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ አገራዊ ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ የልማትና መሰል ተግባራት ላይ እያከናወነችው ያለውን ተግባር ብሎም የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ በመትከል ማንሰራራት በሚለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በሙያቸው ከሚያከናውኑት ተግባር በተጨማሪ አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልካም አጋጣሚን እንደፈጠረላቸው ነው የሚናገሩት።

ጋዜጠኛ ሚኪያስ ጎቡ በሰጠው አስተያየት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት እየተካሔደ ባለው አረንጓዴ አሻራ ኢዜአ በተለያዩ ኹነቶች ላይ በመገኘት ከሚሰጠው ሽፋን በዘለለ የተቋሙ ሰራተኞች የራሳቸውን አሻራ የሚያኖሩበትን እድል አመቻችቷል ነው ያለው።


 

ዛሬ በተካሔደው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ መሳተፉ ከሙያዊ ተግባሩ በዘለለ አገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ምቹ እድል እንደፈጠረለት ገልጾ፤ በቀጣይም በእነዚህና መሰል ተግባራት ላይ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንደሚወጣ አረጋግጧል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጋዜጠኛ አንዱንሰው ሽፈራው በበኩሉ፤ ይህ መርሃ ግብር ባለሙያው በአረንጓዴ አሻራ እንዲሳተፍ እድል የፈጠረለትና በአገር ሁለንተናዊ የልማት ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲጨምር ያገዘ መሆኑን ገልጿል።


 

ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት የተቋሙ ሰራተኞች ወይዘሮ ፍሬህይወት ደምሴ እና እንዳለ ሃይለ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚተላለፍ ሃብት መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የተቋም ተልዕኮ ከማሳካት በዘለለ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለው ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም