በኢትዮጵያ ካሉት አገር በቀል ነባር የስንዴ ዝርያዎች የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ተለይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ካሉት አገር በቀል ነባር የስንዴ ዝርያዎች የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ተለይተዋል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 26/ 2017 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ካሉት አገር በቀል ነባር የስንዴ ዝርያዎች መካከል የተሻለ ምርት የሚያስገኙ አራት የስንዴ ዝርያዎች ተባዝተው ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ዝግጅት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች በተለይ በስንዴ ምርት ላይ የታየው እመርታ ከፍተኛ ነው።
መንግስት ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ማስገባት የለባትም የሚል አቋም ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱን አውስተው፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ስንዴ አምራች ሀገር እንድትሆን አስችሏታል ሲሉ ነው የገለጹት።
በስንዴ ልማት በመኸር እና በበጋ መስኖ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሏልም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን በመቻል ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ያሟላች ሲሆን፤ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ የስንዴ ምርትን በተሻለ መልኩ እንዲያለማ ለማድረግም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ መካከል የስንዴ ዘርን ከነባር ዝርያዎች መካከል የተሻለ ምርት የሚያስገኙ፣ ድርቅና በሽታን የሚቋቋሙ ምርቶች መለየታቸው ነው የተገለጸው።
በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የአዝርእት እና ሆርቲካልቸር ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ውብሸት ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት አራት ነባር የስንዴ ዝርያዎች በማሳ ላይ ተሞክረው የተሻለ ውጤት አስገኝተዋል።
ዝርያዎቹ ለተከታታይ ዓመት ሙከራ እንደተደረገባቸው አመልክተው፤ ድርቅና በስንዴ ምርት ላይ የሚከሰት የዋግ በሽታን ለመቋቋም የሚችሉ መሆናቸው መረጋገጡን ነው የተናገሩት።
በሙከራ የተለዩት አገር በቀል ነባር የስንዴ ዝርያዎች በሔክታር እስከ 58 ኩንታል የሚሰጡ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህም በማሳ ላይ ተዘርቶ ከተገኝው ተጨባጭ ውጤት ለማወቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን በማረጋገጥ ሂደት አገር በቀል ነባር የስንዴ ዝርያዎች በዘርፉ የተመዘገበውን ስኬት ዘላቂ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።
የስንዴ ዝርያዎቹ ከማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞም ውጤታማ ነው ያሉት መሪ ስራ አስፈፃሚው፤ወጪ ቆጣቢና ከአርሶ አደሩ ባለፈ አገርን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አገር የስንዴ ምርትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱ አበረታችና ውጤት የተገኝበት መሆኑ ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ የመሰከረለት እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ባላት እምቅ አቅም አሁን ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች በተሻለ መልኩ የስንዴን ምርት በማሳደግ ከአካባቢው ካሉት አገራት የተሻለ ፀጋ የተቸረች አገር መሆኑዋንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከተመሰረተ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ92 ሺህ በላይ አገር በቀል ነባር ዝርያዎችን መሰብሰቡን ነው ያመለከቱት።